በሌሎች ተክዶ ራሱንም የካደው ትውልድ

የዘመናዊ  ትምህርት  ወይም  “ቀለም  ቀመስ”  የሆነው  የዐማራው  ትውልድ  በሌሎች  ነገዶች/ጎሣዎች  ቀለም  ቀመስ ትውልድ  ተክዷል።  በሌሎች  መካዱን  ያልተረዳውና  ሊረዳም  ያልፈለገው  ቀለም  ቀመሱ  የዐማራ  ትውልድ፣  የራሱን  ማንነት ክዶ  የገዛ  ትውልዱን  ከጥፋት  ለመከላከል  የሚያስችለውን  አቅሙን  ላለመጠቀም  የተለያዩ  ምክንያቶችን  በመደርደር  ራሱንና ወገኖቹን ለጥፋት አጋልጦ፣ “የራሷ ሲያርባት የሰው ታማስላለች” ዓይነት ሆኖ ይታያል። ልብ እንበል ፣ ልብ በሉ! የኢትዮጵያ  ቀለም  ቀመስ  የሆነው  ትውልድ  ፣  በ1960ዎቹ  “መሬት  ላራሹ!”  የሚለውን  መፈክር  ሲያነሣ፣  በመካከሉ ልዩነት  አልነበረም።  በ”መሬት  ላራሹ”  መፈክር  መሪነት  ሕዝባዊ  ትግሉ  እየገፋ  ሲሄድ  ቀለም  ቀመሱን  ትውልድ  በአቋም ከሁለት  የከፈለ  መሠረታዊ  ጥያቄ  ተነሣ።  ያም  ጥያቄ፦  “የኢትዮጵያ  መሠረታዊ  ችግር  ምንድን  ነው?”  የሚለው  ነበር።  ለዚህ ጥያቄ  ሁነኛ  መልስ  ለመስጠት  በተደረገ  የኃሣብ  ፍጭት  ሁለት  ʻበሰሜንና  ደቡብ  ያህል  ተራርቀው  የቆሙʼ  አቋሞች  ጎልተው ወጡ።  አንደኛው  አቋም  “የኢትዮጵያ  መሠረታዊ  ችግር  ብሔራዊ  ጭቆና  ነው፤  ጨቋኙም  የዐማራ  ነገድ  (በእነርሱ  ቋንቋ ብሔር)  ነው፤  የዐማራው  ነገድ  ሲወገድ  ችግሩ  ይፈታል፤”  ከሚል  መደምደሚያ  ደረሰ።  ሁለተኛው  ጽንፍ  ደግሞ፦ “የኢትዮጵያ  መሠረታዊ  ችግር  የመደብ  ልዩነት  ነው፤  ጨቋኝ  መደቦች፣  በተለይም  ገዥው  ጨቋኝ  የዐማራ  መደብ  ሲወገድ የኢትዮጵያ  ችግር  ይፈታል፤”  ብሎ  አመነ።  እንደ  አለመታደል  ሆኖ  በሁለቱም  አቋሞች  የተለያየ  ስም  ይሰጠው  እንጂ፣ እንዲጠፋ  የተፈረደበት  የዐማራው  ነገድ  ነበር፣  ነውም።  ስለዚህ  ዛሬ  በዐማራው  ነገድ  ላይ  እየተፈጸመበት  ያለው  የዘር ማጽዳት ዘመቻ የተጠነሰሰው በዚያን ወቅት እንደነበር የድርጊቱ ሂደት ቁልጭ አድርጎ ያሳያል።  የነበረውን  የአቋም  ልዩነት  ተከትሎ  “ሕዝባዊ  እንቅስቃሴውን  እንመራዋለን”  ያሉ  ድርጅቶች  ብቅ  አሉ።

በመጀመሪያው አቋም ዙሪያ የተኮለኮሉት፦

(1)  በቅኝ  ገዥዎች  ዓላማ  የተጠመቁትና  “ኤርትራ  በኢትዮጵያ  ቅኝ  ግዛትነት  ተይዛለች፣  ከቅኝ  ገዥዋ  ከኢትዮጵያ  ነፃ መውጣት አለባት”ብለው የተነሱት  ጀብሃና ሻዕቢያ፣
(2)   ትግራይን በመገንጠል “የትግራይን ሪፐብሊክ እመሠርታለን” ያለው ሕወሓት (ወያኔ)፣
(3)  “የዐማራው  ነገድ  ኃይማኖታችንን  ፣  ባህላችንን  እና  ቋንቋችንን  አጥፍቷል፣  በመሆኑም  ዐማራው  ከሚያስተዳድራት የአቢሲኒያ  ኢምፓዬር  ነፃነታችን  ማግኘት  አለብን፣”  ያለው  ኦነግ  እና  በዚህ  አቋም  ዙሪያ  የተደራጁት  የነገድና  የጎሣ ድርጅቶች ነበሩ።

በሁለተኛው አቋም ዙሪያ ተሠባስበው የነበሩት ደግሞ፦
(1)  የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ)፣
(2)  የመላው ኢትዮጵያ ሶሻሊስት ንቅናቄ (መኢሶን)፣
(3)  በኢማሌድኅ  ሥር  የታቀፉት  ድርጅቶች፦  አብዮታዊ  ሠደድ፣  ወዛደር  ሊግ፣  ማሌሪድ  እና  ኢጭአት  ሆነው እናገኛቸዋለን።

ይህ  ሁለተኛ  ስብስብ  በመሠረታዊው  ጥያቄ  ዙሪያ  አንድ  ዓይነት  መልስ  ቢኖረውም፣  በችግር  አፈታቱ  ታክቲክ  አመራረጥ ረገድ  ድርጅቶቹ  የተለያዩ  መንገዶችን  መረጡ።  በዚህም  የተነሣ  “የአገሪቱ  መሠረታዊ  ችግር  ነው”  ላሉት  “የመደብ  ልዩነት”  ጉዳይ  አጥጋቢ  መልስ  አልሠጡም።  ከዚያ  ይልቅ  አንዱ  ሌላውን  አሸንፎ  የበላይ  ሆኖ  ለመውጣት  ከፕሮፓጋንዳ  አልፎ  እስከ ትጥቅ ትግል ባደረጉት ግብግብ እርስ በራሳቸው በመጠላለፋቸው አጥፊና ጠፊ ሆኑ። የተፈጠረውም ግብግብ ከአባሎቻቸው አልፎ ለአንድ ዘመን የኢትዮጵያ ወጣት ትውልድ ዕልቂት ምክንያት ሆነ።  በዚያን ዘመን በአቋም ደረጃ ሁሉም ኃይሎች የተስማሙበት አንድ መሠረታዊ ነጥብ “ጨቋኙ ገዥ መደብ የወጣው ከዐማራው  ነገድ  ነው።  ስለዚህ  የዐማራው  ነገድ  የበላይነት  መሠበር  አለበት፤”  የሚል  ነበር።  ይህንን  መፈክር  አንግበው የዐማራውን ነገድ ተወላጆች የኃብትና የፆታ ልዩነት ሣያደርጉ እያደኑ ጨፈጨፏው። ይህም ዕርምጃ ውሎ አድሮ ለኢትዮጵያ ዘብ  ቆሞ  የኖረውን  የዐማራውን  ነገድ  ኃይል  አዳከመው።  በተቃራኒው  ፀረ-ኢትዮጵያ  አቋም  ለያዙት  ብሔርተኛ  ድርጅቶች ብርታትንና ጉልበትን በማጎናጸፍ የፈለጉትን ኢትዮጵያን የማፈራርስ ድርጊት እንዲገፉበት ሠፊ ዕድል ሰጣቸው። በሌላ  በኩል  ደግሞ  “የኢትዮጵያ  መሠረታዊ  ችግር  ብሔራዊ  ጭቆና  ነው፤  ጨቋኙም  ዐማራው  ነው፤”  ብለው የተነሡት  የነገድና  የጎሣ  ድርጅቶች  በአቋማቸው  ፀንተው  ሲቆሙ፣  የዐማራው  ነገድ  ልጆች  ግን  በአቋም  ከሁለት፣  በታክቲክ ረገድ  ከሁለት  በላይ  በሆኑ  ቡድኖች  ተከፋፍለው  ቆሙ።  ለዚህ  አስተዋፅዖ  ያደረገው  የኤርትራ  ገንጣይ  ቡድኖች  አባሎች የብሔራዊ  ፖለቲካ  እንቅስቃሴ  ያደርጉ  በነበሩት  ድርጅቶች  ውስጥ  ሠርገው  በመግባት  የሩቅ  ግባቸውን  ለማሣካት  ያደረጉት አሻጥር  ነው።  በጀብሃና  በሻቢያ  እምነት  ትግላቸው  የሠመረ  የሚሆነው፦  ʻየትውልዱን  የኢትዮጵያዊነት  መንፈስ  አዲስ-ገብ በሆነው  የማርክሣዊ-ሌኒኒናዊ-ማዖአዊ  ርዕዮተ-ዓለም  በማደንዘዝ  የራሱን  ማንነት  አስትቶ  የሌሎችን  ባዕድ  ማንነት እንዲከናነብ  ሲደረግ፤  ጠንካራ  ማዕከላዊ  መንግሥት  ሲዳከም፤  በነገዶችና  በጎሣዎች  መካከል  የነበረው  ነባር  የአንድነት  እና የአብሮነት  ስሜት  ሲላላ፤  “ለኢትዮጵያ  አንድነት  ጠበቃ  ነው”  ብለው  የሚወነጅሉትን  የዐማራው  ነገድ  ሌሎች  ነገዶች በጠላትነት  ፈርጀው  ያለ  የሌለ  ኃይላቸውን  እንዲያነሱበት  ሲደረግ፤  በኢትዮጵያ  አንድነት  የሚያምነው  ኃይል  እንዲከፋፈል ማድረግ  ሲቻል  ነው፤ʼ  ብለው  ሥልታቸውንና  ታክቲካቸውን  ነድፉ።  የዐማራው  ነገድ  ቀለም-ቆጠር  ትውልድ  ግን የተደገሠለትን  ሣያውቅ  “አያ  በሬ ሆይ፣  ሣሩን  አየህና  ገደሉን  ሳታይ፤”  ሆኖበት  በተገንጣዮቹና  ብሔርተኞቹ  ወጥመድ  ውስጥ ሰተት  ብሎ  ገባላቸው።  ይህም  አካሄድ  የጠነከረ  የኢትዮጵያዊነት  አቋም  የነበራቸውንና  ያላቸውን  የዐማራውን  ነገድ  ልጆች አሠናክሎ  በአንድ  መሶብ  እንዳይመገቡ፣  ባንድ  ኮዳ  እንዳይጠጡ፣  በአንድ  እንዳይመክሩና  እንዳይዘክሩ፣  በአንድ  ቃል እንዳይቆሙ አደረጋቸው።

የሚያሣዝነውና  የሚያስቆጨው  በዐማራው  ነገድ  ልጆች  መካከል  “በዘመነ-አብዮት”  የተዘራው  የጠላትነት  ስሜት ዛሬም  አልደበዘዘም።  ከሁሉም  የሚያሣዝነው  ደግሞ  የሁሉም  ቡድኖች  የርዕዮተ-ዓለም  ካባ  የነበረው  ማርክሲስዝም-ሌኒኒዝም-ማዖኅዝም  እንደ  ʻአጥፊ  አመለካከትʼ  ተቆጥሮ  በዓለም  ዙሪያ  ተወግዞ  ተትቷል።  የርዕዮቱ  ግንባር-ቀደም  አራማጅና አስፋፊ የነበረችው ሶቪዬት ኅብረት፣ ርዕዮቱን ጭራሹኑ ከመተው አልፋ፣ በሥሯ የነበሩት የተለያዩ ግዛቶቿ ተገነጣጥለው 15  ራሣቸውን  የቻሉ  አገሮች  ከተፈጠሩ  ከ20  ዓመታት  በላይ  ሆኗቸዋል።  የማዖ  ዜዱንግ  አገር  ሕዝባዊት  ቻይና  ኮሚኒዝም ለአገዛዝ  እንጂ  ለኢኮኖሚ  ብልፅግና  እንደማይበጅ  ተገንዝባ  በቅይጥ  ፍልሥፍና  መመራት  ከጀመረች  30  ዓምታት  አለፋት። የኛዎቹ የዐማራው ነገድ ልጆች ግን “ጅልና ወረቀት ያስያዙትን አይለቅም” ሆኖባቸው ዛሬም ያ ተምኔታዊ ʻየመደብ ጠላትነትʼ ስሜታቸው ከኅሊናቸው ባለመውጣቱ ይቅር ለመባባልና በአንድነት ለመቆም አልቻሉም።  በሌላ አቅጣጫ ሲታይ ደግሞ በፖለቲካ ትግል የአንዱ ቡድን ድክመት ለተቀናቃኙ የጥንካሬ ምንጭ ነው። በዚህም ረገድ  በነገድና  በጎሣ  ልዩነት  ሥር  የተደራጁት  ቡድኖች  ትላንት  እነርሱ  አብረው  ያነሱትን  “የመሬት  ላራሹ” መፈክር በግንባር ቀደምትነት  ተሸክሞ  የጮኸውን  እና  ወላጆቹን  ሰድቦ  ለሰዳቢ  የሰጠውን  የዐማራውን  ነገድ  ልጆች  የትግል  አስተዋፅዖ
ክደውታል።  አልፈው  ተርፈውም  የየራሳቸውን  የሥልጣን  ድርሻ  ይዘው  በየጎሣቸውና  በየነገዳቸው  ሠንደቅ  ዓላማቸውን እያውለበለቡ  ጎጆ  ወጥተዋል።  ይህንን  ሲያደርጉ  ካለምንም  ኃፍረትና  ይሉኝታ  የዐማራውን  ነገድ  ልሂቃን  “አናውቃችሁም  ፣ ከየጎጇችን  ውጡልን”  ብለው  ማረፊያ  ዛፍ  ያጣ  ጉሬዛ  አድርገዋቸዋል።  ነገር  ግን  ዛሬም የአንድ የዐማራው  ነገድ  ልጆች፣  ድሮ በአንድ  ክፍል  የተማሩ፣  በአንድ  ማዕድ  የተመገቡ፣  ውኃ  ተራጭተው፣  አፈር  ፈጭተው  አብረው  ያደጉ  ሰዎች  ከሁሉም አቅጣጫ ለሚደርስባቸው ጥቃት በአንድነት መቆም  አልቻሉም። ብሔርተኞቹ የዐማራውን ልሂቃን ከፋፍለው በመጨረሻም ክደው፣ አገራቸውንና ነገዳቸውን ለማጥፋት ረጅም ርቀት መጓዛቸውን እያዩ፣ በሌሎች ነገዶች ልሂቃን መከዳታቸውን እንኳን ካለመገንዘባቸውም ሌላ፣ ማንነታቸውን ባስካደው ጎዳና እስከመጨረሻው ለመጓዝ የወሠኑ ይመስላሉ።  የዐማራው  ልሂቃን  ʻራስን  የመካድ  አባዜʼ  ዋና  መገለጫው  ሌላ  ምንም  ሳይሆን  የዐማራው  ነገድ  በወያኔ  አገዛዝ ላለፉት  22  ዓመታት  እየደረሰበት  ያለውን  የዘር  ማጥፋት  እርምጃ  ልጆቹ  እንዲታደጉት  ለሚያቀርበው  የተደጋገመ  ጥሪ ʻየዝሆን  ጀሮ  ስጠኝʼ  ማለታቸው  ነው።  እንዲያውም  የዐማራው ምሁር  የበቀለበት  የራሱ  ነገድ  ʻእንደ  ክፉ  አድራጊʼ  ከመወገዝ አልፎ  ሲገደል፣  ሲታሰር፣  ከሥራ  ሲፈናቀል፣  በአገሩ  አትኖርም  ተብሎ  ሲባረር  እያየ  ʻለምን  እንዲህ  ይደረጋል?ʼ  ለማለት  ወኔ አጥሮት  ይታያል።  የወኔው  እጥረት  ምክንያትም  ሌላ  ሣይሆን  የዐማራው  ነገድ  ምሁራን  በሌሎች  መካዳቸውን፣  ነገዳቸው በሁሉም  ነገድ  ልሂቃን  በጠላትነት  ተፈርጆ  እንዲጠፋ  የተከፈተበትን  ዘመቻ  በተከተሉት  የመደብ  ማጽዳት  ርዕየተ-ዓለም የተነሣ  ʻዐማራውን  በገዥ  መደብነትʼ  አብረው  ፈርጀው  እንዲጠፋ  የተስማሙና  እነርሱም  ራሳቸውን  የካዱ  ከመሆኑ  የመነጨ ሊሆን  እንደሚችል  መገንዘብ  አይገድም።  ይህ  ባይሆንማ  ኖሮ  የቀረው  ቢቀር  ስብሐት  ነጋ፣  ዐባይ  ፀሐዬ፣  ሣሞራ  የኑስ  እና ሌሎችም  ቀንደኛ  የወያኔ  መሪዎች  በመደጋገም  “ዐማራውን  ገድለን  ቀብረነዋል”  ሲሉ፤  ዐማራው  ʻበደቡብ፣  በምሥራቅና በምዕራብ  ኢትዮጵያ  መኖር  አትችልምʼ  ተብሎ  ሲባረር፤  ʻለምን?  እንዴት?ʼ  ብሎ  መጠየቅ  የአባት  ነበር።  የዐማራው  ነገድ ቀለም  ቆጠር  ትውልድ  ይህን  ሲያደርግ  አለመታየቱና  አለመሰማቱ፣  በሌሎች  ነገዶች  ልሂቃን  ተክዶ  እንኳን  ራሱንም  የካደ፤ እንዲሁም  የያዘውና  እያራመደው  ያለው  አቋም  ካሉት  ከነባራዊ  ሁኔታዎች  ጋር  ያልተገናዘበ  እንቅስቃሴ  እንደሆነ  ያስረዳል። ድርጊቱ  የራስን  ጥላ  የመሸሽ፣  ማንነትን  በቅጡ  ያለመገንዘብ፣  ከታሰረበት  የድርጅትና  የአመለካከት  እሥር  ቤት  ለመውጣት ፈቃደኛ ያለመሆን አመልካች ነው።

እኒህ  የዐማራው  ልሂቃን  ከዚህም  አልፈው፦  “በዐማራነት  መደራጀት  ዘረኛ  መሆን  እና  ወያኔ  በከፈተው  ቦይ  ገብቶ መፍሰስ  ነው፣  ወዘተርፈ”  በማለት  ተደራጅተው  ጥቃቱን  ለመመከት  በመፍጨርጨር  ላይ  የሚገኙትን  የገዛ  ወገኖቻቸውን ያወግዛሉ።  አልፈው  ተርፈውም  ለዐማራው  ኅልውና  መቀጥል  ተደራጅተው  በመታገል  ላይ  የሚገኙት  ኃይሎች  ተቀባይነት እንዳይኖራቸው የተለያዩ መሠናክሎችን እያጠመዱባቸው ይገኛሉ። በሌሎች  ነገዶች ልሂቃን  ተክደው፣ ራሣቸውንም የካዱት የዐማራው ልሂቃ ያልተረዱት አንድ ነገር ቢኖር፦ ኢትዮጵያን በማጥፋት፣ ከኢትጵያዊነት እምነቱና ከዜግነቱ እየለየው ያለው የትግሬ-ወያኔ  አገዛዝ  ግቡን  ከማሣካቱ  በፊት  ፣  ኢትዮጵያ  መጥፋት  የለባትም።  ለኢትዮጵያና  ለኢትዮጵያዊነት  መቀጠል ምሦሦ የሆነው የዐማራው ነገድ በተያዘው የዘር ማፅዳት ዘመቻ ከጠፋ፣ ኢትዮጵያ አትኖርም። ስለሆነም ኢትዮጵያን ለማዳን “ኢትዮጵያዊ ነኝ” ብሎ ያመነው የዐማራው ነገድ ራሱን አደራጅቶ በመጀመሪያ የራሱን ኅልውና ማስጠበቅ አለበት።
ከ1950ዎቹ  አጋማሽ  እስከ  ጀምሮ  ያለው  የኢትዮጵያ  ቀለም  ቆጠር  ትውልድ  “የአገሪቱ  መሠረትዊ  ችግር  ምንድን ነው?”ብሎ ላነሣው ጥያቄ  ሁለት የተለያዩ ምክንያቶችንና መልሶችን ሰጥቶ በመልሶች ልዩነት ምክንያት ከሁለት መከፈሉ ከፍ ሲል ተጠቅሷል። በተሰጡት ሁለት መልሶች ዙሪያ የተሰለፉት የፖለቲካ ቡድኖች በለስ ቀንቷቸው የፖለቲካ ሥልጣን ይዘው ለችግሩ መፍትሔ ይሆናሉ ያሏቸውን መፍትሔዎች በተግባር አውለዋል። ሆኖም ያቀረቧቸው መፍትሔዎች የአገሪቱን ዜጎች ችግሮች  በማቃለል  ፈንታ  እንዲያውም  ሁኔታዎችን  እጅግ  ወደተወሣሠበ  አዘቅት  የሚያሠምጥ  ሆኗል።  “ግን  ለምን?”  ተብሎ ቢጠየቅ  ችግሮቹ ከመቃለል  ይልቅ የተባባሱበት  መሠረታዊ  ምክንያት፦  ቀለም  ቀመሱ  ትውልድ  የአገሪቱ  መሠረታዊ ችግሮች መነሻ “የመደብ ልዩነትና ብሔራዊ ጭቆና ነው” ሲል የሰጠው መልስ ፍፁም የተሳሳተ በመሆኑ ነው። ማንም መሠረታዊ የሆነ የአመክንዮ  (ሎጂክ)  ዕውቀት  ያለው  ሰው  ሊገነዘበው  እንደሚችለው፣  ከስሕተት  የመነሻ  ኃሣብ  ላይ  ተነስቶ  ትክክል  የሆነ መደምደሚያ  ላይ  መድረስ  አይቻልም።  ወይም  ደግሞ  ከውሸት  ምክንያት  ላይ  ተነስቶ  እውነተኛ  መፍትሔ  ላይ  መድረስ አይቻልም።  በአብዮቱ  መጀመሪያ  ጊዜም  ሆነ  ዛሬ፣  የመደብና  የነገድ/ጎሣ  ልዩነት  የኢትዮጵያ  ሕዝብ  መሠረታዊ  ችግሮች አልነበሩም  ፣  አይደሉምም።  ቀለም  ቀመሱ  ትውልድ  ለአገሪቱ  ሕዝብ  ችግሮች  የሰጠው  መልስ  መለያየት  በራሱ፣  ትውልዱ የአገሩን  ታሪክና  ነባራዊ  ሁኔታዎች  በቅጡ  ያላወቀ  መሆኑን  ከማስረዳት  ባሻገር፣  የተሰጡት  መልሶች  ርዕዮተ-ዓለማዊ አመለካከትን እንጂ፣ የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታዎች መነሻ ያላደረገ መሆኑን ያሣያል። ስለሆነም በሁለቱም ቡድኖች የተሞከሩት መፍትሔዎች ተሞክረው የተገኘው ውጤት የተፎከረለት “እኩልነት ፣  ፍትህ  ፣ ሰላም ፣ ፈጣን ዕድገት ፣  ወዘተርፈ የተጎናፀፈ ሕዝብ”  ሣይሆን  በዓለም  ዙሪያ  ካሉ  የምድራችን  ኗሪዎች  በሙሉ  ʻበችጋር  ፣  በረሃብ  ፣  በሥደት  ፣  በድንቁርና  ፣  በሰብዓዊ መብት ረገጣ የሚማቅቅ ፣ እጅግ ኋላቀር ሕዝብ ፣ ወዘተርፈʼ ዜጎች ያሏትን አገር ነው።   በእርግጥ የኢትዮጵያን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ  እና የማኅበራዊ ዕድገት ታሪክ በቅጡ የሚያውቅ ሰው፣ ትናንትም ሆነ ዛሬ፣ የኢትዮጵያ መሠረታዊ ችግሮች “የመደብ ልዩነትና ብሔራዊ ጭቆና”ያለመሆናቸው ከላይ ተመልክቷል። ስለዚህ የአገሪቱ ችግሮች  የሚፈቱት  “ጨቋኝ  መደብና  ብሔር/ብሔረሰብ”  የተባሉትን  በመደምሰስና  በማጥፋት  አይሆንም።  ትክክለኛው የመፍትሔ  አቅጣጫ  በኢትዮጵያ  በሕግ  የበላይነት  የሚገዛ፣  የግለሰብ  ነፃነትና  መብት  የተረጋገጠበት፣  የግል  ኃብት የተከበረበትና  ዋስትና  የሚያገኝበት፣  የመንግሥት  ሥልጣንና  ኃላፊነት  በምርጫ  ውድድር  ከሕዝብ  ድምፅ  የሚመነጭበት፣ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትና ተቋሞች በመገንባት ነው። ቀለም ቀመሱ ትውልድ ላለፉት 40 ዓመታት እርስ በራሱ የተጠፋፋውና አሁንም ከመጠፋፋቱ የስሕተት ሂደት ሊላቀቅ ያልቻለው አንዴ የተቀበለውን የማርክሣዊ-ሌኒናዊ-ማዖአዊ ርዕዮተ-ዓለም ልክ እንደ ኃይማኖት ቀኖና የማይቀየር ዕውነት አድርጎ በመውስዱና ካለፈው የስሕተት ጉዞው ሊማር የማይፈልግ በመሆኑ ነው።

እንደዚያ  ባይሆንማ  ኖሮ  በኢትዮጵያ  ዕድገት  እንኳን  ባይገኝ፣  ቢያንስ  የነበረንን  ማስጠበቅ  ይቻል  ነበር።  ስለሆነም  የዛሬው ወጣት  የተማረ  ትውልድ  ከእርሱ  በፊት  የነበረው  ቀለም  ቀመስ  ትውልድ  የተጓዘበትን  የስሕተት  ጎዳና  ጠብ  እርግፍ  አድርጎ በመተው አዲስ ራዕይ ሠንቆ፣ አዲስ ጎዳና መቀየስ ይጠበቅበታል። ለዚህም ለአገሪቱ  ሕዝብ መሠረታዊ ችግሮች መንስኤዎች ምን  እንደሆኑ  ከታሪካዊ  ዳራ  ተነስቶ፣  ሣይንሳዊ  በሆነ  መንገድ  በማጥናት፣  ትክክለኛ  ወደሆኑት  መፍትሔዎች  መድረስ ይኖርበታል። የችግሮቹ መሠረታዊ ምንጮች ምን እንደሆኑ በትክክል ካልታወቀ፣ ተገቢ መልስ ላይ መድረስ አለመቻሉ ገሃድ ነው።  ምክንያቱም  ያለፈውም  ቀለም  ቀመስ  ወጣት  አብዮተኛ  ትውልድ  እርስ  በእርሱ  ፊትና  ጀርባ  ከመቆሞ  አልፎ  ደም ያቃባው  ለመሠረታዊ  የአገሪቱ  ሕዝብ  ችግሮች  መንስኤዎች  ናቸው  የተባሉት  ምንጮችና  የተሰጡት  መፍትሔዎች  ስሕተት በመሆናቸው ነው።

ማንም  ንጹሕ  ኅሊና  እና  አስተዋይ  ልቦና  ያለው  ሰው  ሊገነዘበው  እንደሚችለው፣  ዛሬም  ሆነ  ትናንት  የነገድ/ጎሣም ሆነ  የመደብ  ልዩነት  የአንድ  አገርና  ሕዝብ  መሠረታዊ  ችግሮች  ሆነው  የሚታዩ  አይደሉም።  ምክንያቱም  ሁለቱም  የነባራዊ ማኅበራዊ ዕድገት ሂደት ውጤቶች በመሆናቸው፤ ከሰዎች ፍላጎት ውጪ በምርት ኃይሎች ዕድገት ሣቢያ የሚፈጠሩ ስለሆኑ፤ “አያስፈልጉም፣ ይወገዱ፣ ይጥፉ” ቢባሉ እንኳን በመፈክር ብዛት በማውገዝና የተወሠነውን “ጠላት” ተብሎ የተፈረጀ የአንድ አገር  የሕዝብ  ክፍል  በመፍጨፍጨፍ  ብቻ  በፍፁም  ሊወገዱ  ስለማይችሉ  ነው።  ስለሆነም  የመደብና  የነገድ/ጎሣ  ልዩነቶች የነባራዊ  ዕድገት  ሂደት  ውጤቶች  መሆናቸውን  አውቆና  አምኖ  መቀበል  ያስፈልጋል።  የሚሻለው  አማራጭ  አንዱ መደብ/ነገድ/ጎሣ  በሌሎች  ላይ  ጤናማ  ያልሆነ  ተፅዕኖ  እንዳያሣድር  ፖለቲካዊ፣  ኢኮኖሚያዊና  ማኅበራዊ  ግንኙነቶች  ተገቢ ሚዛናቸውን  ጠብቀው  እንዲጓዙ  የሚያስችል  ሁሉም  ዜጎች  መጫዎት  ያለባቸውን  ድርሻ  በሥርዓት  እንዲወጡ  የሚያደርግ የመልካም አስተዳደር  ሥርዓት በመዘርጋት  ነው።  በመሆኑም  አንዱን  የሕዝብ  ክፍል  የሆነ መደብ/ነገድ/ጎሣ  ነጥሎ  በማጥፋት ሊገኝ  የሚችል  ሰላምና  መረጋጋት፣  እንዲሁም  ሚዛኑን  የጠበቀ  ዕድገት  ሊመጣ  እንደማይችል  ግልጽ  ሊሆን  ይገባል።  ከዚህ አንፃር  በሌሎች  ተክዶ  ራሱንም  የካደው  የዐማራው  ቀለም  ቀመስ  ትውልድ  ላለፉት  40  እና  50  ዓመታት  የተጓዘበት  የትግል ጉዞ  ለእርሱም  ሆነ  ለትውልዱ  አልፎም  ለአገሩ  ያልበጀ  በመሆኑ፣  ከታሰረበት  የድርጅትና  ግትር  ግራ-ዘመም  ርዕዮተ-ዓለም የቀኖና እሥር ቤት ወጥቶ ወገኑን ከፈጽሞ ጥፋት ሊታደግ ይገባዋል።

ዐማራን ከፈፅሞ ጥፋት እንታደግ!
ፈለገ-አሥራት የተውልዳችን ቃልኪዳን ነው!
ኢትዮጵያን እግዚአብሔር ይጠብቅ!

11/18/2013